Prefer English? Read this guide in English.
ወደ ቤተሰብ ገንዘብ መላክ የሳምንቱ ቀላሉ ሥራ መሆን አለበት። ለብዙዎች ግን እንደዚያ አይደለም። የምንዛሪ ተመኑ ከጠዋት እስከ ማታ ይለዋወጣል፤ ክፍያው እስከ መጨረሻው ገጽ ድረስ በግልጽ አይታወቅም፤ ገንዘቡ መቼ እንደሚደርስም የሚነግርዎ የለም።
ይህ መመሪያ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በBlessedRoots እንዴት ገንዘብ እንደሚልኩ ያሳያል፦ ከመጀመርዎ በፊት የሚያስፈልግዎት፣ ቤተሰብዎ ገንዘቡን የሚቀበልበትን መንገድ እንዴት እንደሚመርጡ፣ የሚታይዎትን የምንዛሪ ተመን የሚወስነው ምን እንደሆነ፣ እና በአሜሪካ ሕግ መሠረት እንደ ላኪ ያሉዎት መብቶች ምን እንደሆኑ።
ከመጀመርዎ በፊት የሚያስፈልግዎት
- ክፍያ የሚፈጽሙበት የአሜሪካ ባንክ አካውንት፣ ዴቢት ካርድ ወይም ክሬዲት ካርድ።
- በመንግሥት የተሰጠ ፎቶ ያለው መታወቂያ። የመጀመሪያ ዝውውርዎ ከመፈጸሙ በፊት ማንነትዎን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል። ይህ የBlessedRoots ፖሊሲ ሳይሆን፣ በአሜሪካ ፈቃድ ባለው በማንኛውም የገንዘብ አስተላላፊ ላይ የሚጣል የፌዴራል ሕግ ግዴታ ነው።
- የተቀባዩ ሙሉ ስም - በኢትዮጵያ ባንክ አካውንቱ ወይም በtelebirr ምዝገባው ላይ በተጻፈበት አኳኋን።
- የባንኩ ስምና የአካውንት ቁጥር፣ ወይም የtelebirr ስልክ ቁጥር።
ዝውውር እንዲዘገይ የሚያደርገው ዋነኛው ምክንያት ከተቀባዩ አካውንት ጋር የማይገጣጠም ስም ነው። ስሙን ከማስታወስ ሳይሆን ከመታወቂያው ወይም ከባንክ ደረሰኙ ላይ ገልብጠው ያስገቡ።
በአራት ደረጃዎች መላክ
- አካውንት ይክፈቱ። በኢሜይልና በስልክ ቁጥር ጥቂት ደቂቃዎች ይወስዳል። ለመጀመሪያ ጊዜ የማንነት ማረጋገጫውን ያጠናቅቃሉ።
- የክፍያ መንገድዎን ያስገቡ። የባንክ አካውንት፣ ዴቢት ካርድ ወይም ክሬዲት ካርድ ማገናኘት ይችላሉ።
- ዝውውሩን ያስገቡ። ኢትዮጵያን ይምረጡ፣ መጠኑን ያስገቡ፣ ተቀባዩ ገንዘቡን የሚቀበልበትን መንገድ ይምረጡ። ከማረጋገጥዎ በፊት የምንዛሪ ተመኑ፣ ክፍያው እና ተቀባዩ የሚደርሰው ትክክለኛ የብር መጠን ይታይዎታል። ይህን ገጽ በጥሞና ያንብቡት። በሕግ እንድንሰጥዎ የሚጠበቅብን መረጃ ነው፤ በዚያ ገጽ ላይ ያለው የብር መጠንም ዋናው ቁጥር ነው።
- አረጋግጠው ይከታተሉ። የዝውውሩን ሁኔታ በቀጥታ መከታተል ይችላሉ፤ ተቀባዩም መልእክት ይደርሰዋል።
በባንክ ወይስ በtelebirr?
ቤተሰብዎ ገንዘቡን የሚቀበልበት ሁለት መንገድ አለ፤ የሁለቱም ዋጋ የተለያየ ነው።
- የኢትዮጵያ ባንክ አካውንት - እኛ ከምንደግፋቸው 33 ባንኮች ወደ አንዱ አካውንት ገቢ ይሆናል። ለከፍተኛ መጠንና አካውንት ላላቸው ተቀባዮች ይመቻል።
- telebirr - ገንዘቡ በቀጥታ ወደ ተቀባዩ የtelebirr ሞባይል ቦርሳ ይገባል። የባንክ አካውንት ለሌላቸው ወይም ከባንክ ቅርንጫፍ ርቀው ለሚኖሩ ይመቻል።
ሁለቱ የተለያየ የምንዛሪ ተመን አላቸው። መተግበሪያው ሁለቱንም ጎን ለጎን ያሳያል፤ ስለዚህ ተመኑን ብቻ ሳይሆን የመጨረሻውን የብር መጠን ያወዳድሩ።
ገንዘቡ በምን ያህል ጊዜ ይደርሳል
አብዛኞቹ ዝውውሮች በደቂቃዎች ውስጥ ይደርሳሉ። የእርስዎ ዝውውር የሚፈጅበት ጊዜ በመረጡት የክፍያ መንገድ፣ በተቀባዩ ባንክ አሠራር፣ እንዲሁም ዝውውሩ ለመደበኛ የተገዢነት ምርመራ ተመርጦ እንደሆነ ይወሰናል።
ከመክፈልዎ በፊት መተግበሪያው ገንዘቡ የሚደርስበትን ቀን ያሳይዎታል። ይህ ቀን በሕግ የምንሰጠውና የምንጠየቅበት መረጃ ነው እንጂ በዝምታ የምናስተካክለው ግምት አይደለም።
ዝውውርን የሚያዘገዩ ነገሮች
- ከተቀባዩ አካውንት ጋር የማይገጣጠም ስም።
- የመጀመሪያ ዝውውር ሲሆን፣ የማንነት ማረጋገጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ።
- በተቀባይ ባንክ በኩል የሥርዓት መቋረጥ ወይም የታቀደ ጥገና።
- በኢትዮጵያ ወይም በአሜሪካ የበዓል ቀናት።
የምንዛሪ ተመኑንና ክፍያውን የሚወስነው ምንድን ነው
ኢትዮጵያ በ2024 ወደ ገበያ ተኮር የምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተሸጋግራለች፤ ስለዚህ የብር ተመን አሁን በአስተዳደራዊ ውሳኔ ሳይሆን በገበያ ሁኔታ ይወሰናል። የእኛም ተመን ገበያውን ተከትሎ በተከታታይ ይታደሳል። ጠዋት ያዩት ተመን ማታ ላይ ያው ላይሆን ይችላል።
- ተመኑ የሚቆለፈው ዝውውሩን ሲያረጋግጡ ነው እንጂ መተግበሪያውን ሲከፍቱ አይደለም።
- የባንክና የtelebirr ክፍያዎች የተለያየ ዋጋ አላቸው፤ ስለዚህ ተመኑን ሳይሆን የብር መጠኑን ያወዳድሩ።
ክፍያዎች እንደ ዝውውሩ ዓይነትና እንደ ክፍያ መንገዱ ይለያያሉ። ክፍያውም ተመኑም ከማረጋገጥዎ በፊት ይታያሉ። ከመክፈልዎ በፊት ጠቅላላ ወጪውን ሊነግርዎ የማይችል አገልግሎት ካጋጠመዎት፣ ከዚያ አገልግሎት ይራቁ።
ከአሜሪካ ገንዘብ ሲልኩ ያሉዎት መብቶች
ከአሜሪካ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች በConsumer Financial Protection Bureau (CFPB) የRemittance Transfer Rule ሥር ይተዳደራሉ። በማንኛውም አገልግሎት ቢልኩ የሚከተሉት መብቶች አሉዎት፦
- ከመክፈልዎ በፊት መረጃ የማግኘት መብት - የምንዛሪ ተመኑን፣ ሁሉንም ክፍያዎችና ታክሶች፣ ተቀባዩ የሚደርሰውን መጠን እና የሚደርስበትን ቀን የሚያሳይ።
- ያለ ምንም ክፍያ ለመሰረዝ 30 ደቂቃ - ከከፈሉ በኋላ፤ ገንዘቡ ገና ካልተወሰደ ወይም ወደ አካውንት ካልገባ።
ከማጭበርበር ራስዎን ይጠብቁ
የገንዘብ ዝውውር ማጭበርበር በተለይ በውጭ አገር የሚኖሩ ቤተሰቦችን ዒላማ ያደርጋል፤ ብዙ ጊዜም ፈቃድ ያለውን እውነተኛ ኩባንያ ስም ተጠቅሞ ነው።
- የይለፍ ቃልዎን፣ ሙሉ የካርድ ቁጥርዎን ወይም የአንድ ጊዜ ኮድ በስልክ፣ በWhatsApp ወይም በTelegram ፈጽሞ አንጠይቅም።
- ሌላ ዝውውር እንዲለቀቅ ወይም እንዲረጋገጥ ገንዘብ እንዲልኩ ፈጽሞ አንጠይቅም። ይህ ጥያቄ ሁልጊዜ ማጭበርበር ነው።
- የሚልኩት በመተግበሪያው ወይም በblessedroots.com በኩል ብቻ ይሁን። አንድ ሰው በግል አካውንት የተሻለ ተመን ቢያቀርብልዎ፣ ምንም ዓይነት ጥበቃ አይኖርዎትም፤ ገንዘቡንም የማስመለስ መንገድ የለም።
- መረጃ ከማስገባትዎ በፊት blessedroots.com ላይ መሆንዎን ያረጋግጡ።
የሆነ ነገር ካላማረዎት ያቁሙና support@blessedroots.com ያግኙን።
እገዛ ሲፈልጉ
በስልክ፣ በኢሜይልና በቻት እገዛ ያገኛሉ፦ support@blessedroots.com
Nyota Financial LLC (BlessedRoots) በFinCEN የተመዘገበ የገንዘብ አገልግሎት ተቋም (MSB #31000302682897) ሲሆን፣ በሜሪላንድ ግዛት በNMLS ID 2707227 ለመሥራት ፈቃድ አለው። የምንዛሪ ተመንና ክፍያዎች ይለዋወጣሉ፤ ከመላክዎ በፊት በመተግበሪያው ላይ ያለውን ወቅታዊ ዋጋ ይመልከቱ። ክፍያዎች እንደ ዝውውሩ ዓይነት ይለያያሉ። መመሪያና ደንቦች ተፈጻሚ ናቸው።